top of page

ኢሴሃማ 1ኛ መደባኛ ስብሰባውን አካሄደ

Updated: May 1, 2020

የኢትዮጵያ ሴት ሃኪሞች ማህበር 2ኛ አመት 1ኛ አመታዊ ጠቅላላ ስብሰባ እሑድ ሰኔ 16 ቀን 2011ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡30 ላይ በሂልተን ሆቴል ‘Empower Women Raise the Nation’ በሚል መሪ ቃል ተካሄደ፡፡

ለጠቅላላ ጉባዔው ሃምሳ አራት (54) አባላት በመገኘታቸው ምልዐተ ጉባዔው መሟላቱ ከተረጋገጠ በኋላ የስብሰባው አስተዋዋቂ ዶ/ር ልዕልና ሺመልስ ስብሰባውን በይፋ ከፍተዋል። ተሰብሳቢዎችን እንዃን ደህና መጣችሁ ካሉ በሁዋላ በእለቱ በአገሪትዋ በተከሰተው አሳዛኝ ክስተት የተሰማቸውን ሃዘን ገልፀዋል። በመቀጠልም የማህበሩን 1ኛ አመታዊ ጠቅላላ ስብሰባ በይፋ እንዲከፍቱ የጠቅላላ ጉባኤው ሰብሳቢ ዶ/ር ሃይማኖት የየሱስወርቅን ወደ መድረክ ጋብዘዋል።


የስብሰባው አጀንዳ የሚከተለው ነበር

1. የ2011 በጀት ዓመት የማህበሩ የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት

2. የማህበሩን አርማ እና የመደበኛ አባላት አመታዊ መዋጮ ተወያይቶ መወሰን

3. አዲስ የስራ አስፈፃሚ አባላት ምርጫ ማካሄድ

4. ጥናታዊ ፅሁፍ እና የማህበሩ የወደፊት አካሄድ ውይይት


ዶ/ር ሃይማኖት የየሱስወርቅ በአገሪቱ የተከሰተውን የፀጥታ ችግር እንዳሳዘናቸው እና በጥብቅ እንደሚያወግዙ ገልፀዋል። በመቀጠልም ማህበሩ የተቆቆመበትን አላማ በመማስታወስ እናም አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል። ዴንክ ፋርማ የኢሴሃማ ለመመስረት ሃሳቡን ከማመጨት ጀምሮ እስከ አባላትን አስተባብሮና ምዝገባውና እውቅና እስከ ሚካሄድ ድረስ ላደረገው ትልቅ አስተዋፆ ያመሰገኑ ሲሆም በመቀጠልም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከጎን ሆኖ ማህበሩን በማበረታታት ላሳየው የገንዘብ ድጋፍ አመስግነዋል። ፕሮፌሰር ሰናይት ፍስሃ በአመራርና በተለያየ መልክ ለሴቶች ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም ለማህበሩ ከምስረታው ጀምሮ ላሳዩት ቅን ተሳትፎና ድጋፍ ምስጋናቸውን አስተላልፈዋል። በመጨረሻም ማህበሩ ከተቆቆመበት ግዜ አንስቶ ካላቸው የተጣበበ ጊዜ ቀንሰው ማህበሩን በተለያየ መልኩ ሲያገለግሉ ለነበሩት 9 የስራ አስፈፃሚነት ኮሚቴ አባላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በመቀጠልም የማህበሩ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑትን ዶ/ር ነቢያት ሰመረዲን ስለማህበሩ አላማና ራዕይ አጭር መግለጫ እንዲሰጡ ወደ መድረክ ጋብዘዋል።




የስብሰባው አስተዋዋቂ ዶ/ር ልዕልና ሺመልስ ከዶ/ር ነቢያት ሰመረዲን ገለፃ በፊት በእለቱ ለመገኘት ያልቻሉትን የክብር እንግዳ ዶ/ር ሊያ ታደሰ በተወካያቸው በዶ/ር ማህሌት ይገረሙ አማካኝነት መልክታቸውን እንዲያስተላልፉ ጋብዘዋል።


ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ የክብርት እንግዳዋን መልክት በፀሁፍ ከማቅረባቸው በፊት የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት እንዲደረግ የእለቱን ታዳሚዎችን ጋብዘዋል። በመቀጠልም መልክቱን ያነበቡ ሲሆን በዚህም ክብርት እንግዳዋ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ መገኘት ባለመቻላቸው የተሰማቸውን ሃዘን ገልፀዋል። የእለቱ መሪ ቃል የሆነውን “ሴቶችን ጉልበት መስጠት አገርን ማንሳት” የሚለውን ሃሳብ ጠንካራነት እና ወቅታዊነት አውስታውሰው በአገሪቱ እያደገ ላለው የሴት ሃኪሞች ቁጥር ማለትም 200 እና 300 የነበረውና በአሁኑ ወቅት ከ3000 በላይ ለደረሰው የሴት ሃኪሞች ቁጥር አስተዋፀኦ እንደሚኖረው ገልፀዋል። የማህበሩ አባላት እንድም እንደ ሴት ሌላም እንደ ጤና ባለሙያነታቸው ሴት ተኮር የጤና አሰጣጥ ላይ ትኩረት ሰጥተው ብዙ ሊሰራ ይገባል ብለዋል። በተለይ ሴት ሃኪሞች ባሉበት ማንኛውም የስራ እና የህይወት ጉዞ ውስጥ መሪ መሆናቸውን አስታውሰው የሴቶችን በተለያዩ መስኮች እኩል ተሳትፎ ከማምጣት በዘለለ ያላቸውን ልዩ እይታ እንዲያንፀባርቁ ጥሪ አቅረበዋል። በማህበረሰቡ እና በህክምና ሙያ መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላት የሴት ሃኪሞች ድርሻ ትልቅ መሆኑን ገልፀው የማህበሩ አባላት የመሪነት ድርሻዎች ላይ በንቃት እንዲሳተፉና የተሻለ ነገን ለመፍጠር እንዲተጉ አሳስበዋል። በመጨረሻም ሴቶች በተለያየ ቦታ የሚጫወቱት የተለያዩ የሃላፊነት ድርሻ ስላሉባቸው ይህን ለማሳካት እርስ በራሳቸን በመደጋገፍ ብሎም በሃላፊነት ቦታዎች ተጠይቀን ሳይሆን ጠይቀን በመሳተፍ የሴት ሃኪሞችን፤ የሴቶችን እና የእናቶችን ህይወት እንደ አገር ከፍ እናድርግ በማለት መልክታቸውን አስተላልፈዋል።



የስብሰባው አስተዋዋቂ ዶ/ር ልዕልና ሺመልስ በመቀጠልም ዶ/ር ነቢያት ሰመረዲን የማህበሩን ራዕይ፤ አላማና ግቦች እንዲያቀርቡ ወደ መድረኩ ጋብዘዋል።


ዶ/ር ነቢያት ሰምረዲን በእለቱ በአገሪቱ በተከሰተው የፀጥታ ችግር የተሰማቸውን ሃዘን በመግለፅ ንግግራቸውን ከፍተዋል። በመቀጠልም የማህበሩን መስራቾች ከዚህ ጠቅላላ ጉባኤ በፊት የሚያስፈልጉ ቅድመ ዝግጅቶችን ለመወያየት የመጀመሪያ ስብሰባውን በሰኔ 2010 በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ማካሄዱን ገልፀዋል። የኢሴሃማ ከዚህ ቀደም በ2002 እኤአ ተመስርቶ የነበረ ቢሆንም በብዙ ምክንያቶች ከሁለት አመት በሁዋላ መቀጠል አልቻለም። ከ17 አመታት በሁዋላ በድጋሚ ይህን ማህበር ለሴት ሃኪሞች እና ለማህበረሰቡ ያለውን አስተዋፀኦ በመገንዘብ እና በዴንክ ፋርማ በሚባለው ተቆም አስተባባሪነት በመጋቢት 8 2017 እኤአ 13 ሴት ሃኪሞች በተገኙበት በራማዳ ሆቴል ለመመስረት መስማማታቸውን ገልፀዋል። ከዛም በዴንክ ፋርማ ከፍተኛ ድጋፍ በግንቦት 08 2017 እኤአ በመንግስት ተመዝግቦ የምስክር ወረቀት ተሰጥቶታል። የየማህበሩን ራዕይ፤ አላማና ግቦች አቅርበዋል። በዚህ መሰረት ማህበሩ የተቆቆመበት አላማ በኢትዮጵያ ያሉ የሴት ሃኪሞች በእኩል መብት በውሳኔ ሰጪነት ያላቸውን ተሳትፎ በማዳበር ተሰሚነታቸውን መጨመር ነው። እንዲሁም በሁሉም የህይወት እና የጤና ጉዳዮች የህክምና ሴቶች አስተዋፅ, የሚታወቅበት ፣ የሚከበሩበት እና የሚሸለሙበትን መድረክ በህብረተሰብ ለመፍጠር ይፈልጋል ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የማሕበሩ ተልዕኮ ሴቶች በሁሉም መስክ የበኩላቸውን ድርሻ ተሳታፊነት ብሎም ተሰሚነታቸውን መጨመር በሕክምና መስክ በሙያቸው የላቀ ቦታ እንዲደርሱ ማገዝ እና የሴቶች እና የህብረተሰቡ ጤና ለማሻሻል ያላቸውን አስተዋፅኦ ለማሳደግ ነው፡፡አያይዘውም ለሴቶች ሊደረጉ ስለሚታሰቡ የማማከር እና የስልጠና እቅዶች ከገለፁ በሁዋላ፤ የተጠቀሱትን አላማዎች ለማሳካት ማለፍ ስለሚጠበቀው ጠንካራ ሂደት ጠቁመዋል ንግግራቸውን አጠቃለዋል።




የስብሰባው አስተዋዋቂ ዶ/ር ልዕልና ሺመልስ መድረኩን ተረክበው ማህበሩ ተጠናክሮ እንዲሰራና በዶ/ር ነቢያት ሰምረዲን የቀረቡትን የማህሩን አላማ፤ራዕይ እና ግቦች ለማሳካት የአባላቱ ተሳትፎ ወሳኝ እንደሆነና አባላት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ አበረታትተዋል። በመቀጠልም ማህበሩን በመደገፍ ትልቅ አስተዋፀኦ ላበረከቱ ተቁዋማት እና ግለሰቦች የምስጋና ስነስርአት ጊዜ መሆኑን አስታውቀው ሽልማቱን እንዲያበረክቱ ዶ/ር ብዙነሽ እና ዶ/ር ሃይማኖት የየሱስወርቅን ወደ መርረክ ጋብዘዋል።ሰርቲፍኬት የተሰጣቸው አካላት በቅድመ ተከተል የሚከተሉት ናቸው፤

Ø ለDenk Pharma

Ø ለጤና ጥበቃ ሚኒሲቴር

Ø ለፕሮፌሰር ሰናይት ፍስሃ

Ø ለቀድሞ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት(ዶ/ር ቃልኪዳን አላቸው፤ ዶ/ር ሊዲያ ተፈራ፤ ዶ/ር ሙና አብዱልቀድር፤ ዶ/ር ቤቴል ደረጄ፤ ዶ/ር ነቢያት ሰመረዲን፤ ዶ/ር ኤደን ፍስሃ፤ ዶ/ር ሰናይት በየነ፤ ዶ/ር ፍረወይኒ አባይ፤ ዶ/ር ሃይማኖት የየሱስወርቅ፤ ዶ/ር ልዕልና ሺመልስ) ናቸው።




ዶ/ር ሃይማኖት የየሱስወርቅ በማጠቃለያ እነዚህ ግለሰቦች እና ተቁዋማት ነገ ለሚገነባው ጠንካራ ማህበር ካላቸው ጊዜ እና ጉልበት ቆጥበው ብዙ ፈተናዎችን አልፈው እዚህ መድረሳቸውን አስታውሰው በቀጣይ የስብሰባው ተሳታፊዎች በማህበሩ ጉዞ ላይ የተቻላቸውን ተሳትፎ እንዲያበረክቱ ከጎናቸው እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።


ከ5፡00 እስከ 5፣30 ድረስ ጉባኤው ለሻይ እረፈት ተቋረጠ፡፡




ከሻይ እረፍት መልስ የስብሰባው አስተዋዋቂ ዶ/ር ልዕልና ሺመልስ የእለቱ ፕሮግራም ላይ ቶሎ ለማጠናቀቅ ሲባል ማስተካከያ እንደተደረገ ገልፀዋል። በመቀጠልም ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ አይደር ሆስፒታል የመጡ ሴት የinternship ተማሪዎች ከሌሎች የሆስፒታሉ የህክምና ባለሙያዎች ጋር በመሆን በአካባቢያቸው የሴቶችን ጤና ለማሻሻል እያከናወኑዋቸው ያሉትን የተለያዩ ስራዎች ለማህበሩ አባላት እንዲያቀርቡ የቡድኑ ተወካይ ዶ/ር ቤቴልሄም ወደ መድረክ ጋብዘዋል።


ዶ/ር ቤቴልሄም መድረኩን ተረክበው እዚህ ቦታ ላይ ተገኝተው ንግግር ማድረግ በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል። በመቀጠልም የቡድናቸው መጠሪያ አይደር ሜዲካል ዶክተርስ ግሩፕ እንደሚባል እና በታህሳስ 2018 እኤአ በበጎ ፈቃደኛ ኢንተርን ተማሪዎች የተመሰረተ ሲሆን አባላቱም የህክምና ተማሪዎች፤ መምህራን እና ሰራተኞችን ያካተተ ነው። ቡድኑ የተቆቆመው የህክምና ተማሪዎች እርስ በእርስ ለመደጋገፍ ሲሆን እንደ አላማም የተለያዩ የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት በህክምና መምህራን እና ተማሪዎች ያለውን ክፍተት ለመሙላት ብሎም እንደ ሴት የሚገጥማቸውን በጋራ ለመወያየት ታልሞ የተደረገ እንቅስቃሴ ነው። በተጨማሪም የተለያዩ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ የተለያዩ የማህበረሰብ ችግሮችን ለመቅረፍ አስተዋፀኦ አድርግዋል። የመጀመሪያውን ስብሰባ በየሎ ሙቭመንት ረዳትነት ያዘጋጋጀ ሲሆን በውይይቱም ሴት ሃኪሞች ስለሚደርስባቸው ፆታዊ ጥቃት፤ ምቹ ስላልሆነው የስራ ቦታ ሁኔታዎች እና የስራ ቦታ ላይ ጥቃትን ለመከላከል ዩኒቨሪስቲው ስላለው የህግ ማእቀፍ በመገንዘብ ለሌሎች ስለማስተዋወቅ መወያየታቸውን ጠቅሰዋል። በተለያዩ የግንኙነት መድረክ በመጠቀም የሴቶች ወር ማክበራቸውን እና በወሩ መገባደጃ ላይ ሌላ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት እና ሲንየር የሆስፒታሉን ዶክተሮች በመጋበዝ ከመጨረሻ የውይይት መድረኩ የተወሰዱ ሃሳቦችን በግልፅ ከተማሪዎች ጋር የተወያዩ ሲሆን በተለይ በሴቶች ላይ ስለሚደርሰው ፆታዊ ጥቃት በሰፊ መክርዋል። በሁለቱ መድረኮች ማጠቃለያ የተወሰዱት ሃሳዶች ተመርኩዞ በዋነኛነት የፆታዊ ትንኮሳ ላይ ስላለው የህግ ማእቀፍ ግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴዎችን ያደረገ ሲሆን በተጨማሪ ለሴት የህክምና ተማሪዎች የዲውቲ ክፍል እንዲለይ ያደረጉ ሲሆን በዩኒቨሪስቲው የዚህ ቡድን ተጠሪ ሰው በየትምህርት ክፍሉ ለማስቀመጥ ማሰባቸውን አክለዋል። ስለ ሴቶች የወር አበባ ንፅህ አጠባበቅ ላይም በሰፊው እየሰሩ መሆኑን እና በተለያየ መልኩ በዝቅተኛ የኑሮ አቅም ላየ ለሚገኙ ሴቶች የተለያዩ ድጋፎችን ከማሪያም ሰባ የንፀህና መጠበቂያ አምራች ድርጀት ጋር በመተባበርና ማድረጋቸውንና በቀጣይም አጠናክረው ለመቀጠል አላማ እንዳላቸው ጠቅሰዋል። ከላይ የተጠቀሱትን እንቅስቃሴዎችን አጠናክረው ከተለያዩ የትምህርት ክፍላት ጋር ብሎም ከኢሴሃማ በጋራ በመተባበር እና በጋራ በመስራት በህክምና ትምህርት ላይ እናም በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ለሚገኙ ሴቶች የበኩሉን አስተዋፀኦ ለማበርከት የተለያዩ ፕሮግራሞችን ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልፀው ንግግራቸውን አጠቃለዋል።




የስብሰባው አስተዋዋቂ ዶ/ር ልዕልና ሺመልስ መድረኩን ተቀብለው ኢሴሃም ከተቆቆመ ጀምሮ ያከናወናቸውን ተግባራትን ሪፖርት ለማቅረብ ዶ/ር ቃልኪዳም አላቸው ወደ መድረክ ጋብዘዋል።


በዶ/ር ቃልኪዳን አላቸው መድረኩን ተረክበው በድጋሚ በሃገሪቱ በተከሰተው አደጋ የተሰማቸውን ሃዘን ከገለፁ በሁዋላ የማህበሩን ምስረታ አስፈላጊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዴት እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል። በመቀጠልም ወደ ተዘጋጀው ዝርዝር ሪፖርት አልፈዋል። ሪፖርቱ በሶሰት ይዘቶች ላይ ያተኮረ ሲሆን እነሱም፣


1. በ2011ዓ.ም ማህበሩ የተፈራረማቸው የመግባቢያ ሰነዶችና ያገኘው የገንዘብ ድጋፍ

2. በ2011ዓ.ም ማህበሩ ያከናወነው የMentorship TOT ስልጠና

3. በ2011ዓ.ም ማህበሩ ይከናወናቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች

4. በቀጣይ ማህበሩ ሊሰራቸው ስላሰባቸው እንቅስቃሴዎች


1. በ2011ዓ.ም ማህበሩ የተፈራረማቸው የመግባቢያ ሰነዶችና ያገኘው የገንዘብ ድጋፍ።

· ማህበሩ በ2 08 2018 እኤአ ከኢፌዲሪኢ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሙዋል። የስምምነቱ ዋና ዋና ነጥቦችም የቴክኒክ፤ የገንዘብ እና የተቋማዊ ትብብር እና ትስስርን ለመፍጠር ታስቦ ለማድረግ የተፈረመ ነው።

· በዚህም መሰረት በስምምነቱ መሰረት የ320000 USD የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት የተቻለ ሲሆን በዚህም ቃል ከተገባው ድጋፍ 50% ለማህበሩ ገቢ ተደርግዋል።

2. በ2011ዓ.ም ማህበሩ ያከናወነው የmentorship TOT ስልጠና

· ከጤና ጥበቃ በተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ማህበሩ ከስድስት ዩኒቨርስቲዎች ለተውጣጡ ሴት ሃኪሞች የመሪነት(mentorship) የመጀመሪያውን የአሰልጣኞች ስልጠና (TOT) በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ሰጥትዋል።

· በዚህ ስልጠና 16 ሴት ሃኪሞች የተሳተፉ ሲሆን ከስልጠናው በህዋላ በተደረገ የአስተያየት መሰብሰቢያ ቅፅ አበረታች አስተያየት እና ምላሽ ተገኝትዋል።

3. በ2011ዓ.ም ማህበሩ ያከናወናቸው የተለያዩ እንቅስቃሴዎች

· በ በጥቅምት 2011 ዓም የመጀመሪያውን የማህበሩን ፅህፈት ቤት ቢሮ ተከራይትዋል። ፅህፈት ቤቱም የሚገኘው በቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 06 የቤት ቁጥር 9999/1 የኢትዮጵያ ሃኪሞች ማህበር በሚገኝበት ቅጥር ግቢ ውስጥ ነው።

· የማህበሩን ፅህፈት ቤት ለማደራጀት የተለያዩ የቢሮ መገልገያ ቁሶች ተገዝተዋል።

· ከግንቦት 16 – 18 2019 በተካሄደው 5ኛው የኢትዮ ሄልዝ ኤግዚቢሽን ላይ ማህበሩን ለማስተዋወቅ ተሳትፍዋል።

· ለMedical Womens International Aassociation ማህበሩ በአባልነት ለመመዝገብ ጥያቄ ያቀረብን ሲሆን በቅርቡ ምላሽ እንደሚያገኝ ይጠበቃል።

· ማህበሩን በሰው ሃይል ለማደራጀት የዋና ስራ አስፈፃሚ እና የፋይናንስና አስተዳደር ሃላፊ ክፍት የስራ መደብ ማስታወቂያ በ ግንቦት ወር ወጥትዋል።

· የማህበሩን ድህረ ገፅ ለማሰራት እየተሞከረ ሲሆን ከዛ አስቀድሞ ግን የቴሌግራም ቻናል በመክፈት አባላትን ለማግኘት እና መረጃ ለመለዋወጥ እየተሞከረ ነው።

5. በቀጣይ ማህበሩ ሊያከናውናቸው ያሰባቸው እንቅስቃሴዎች

· የተለያዩ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስር የሚዋቀሩ ልዩ ግብረሃይል መማቋቋም የተለያዩ ተግባራትን ማከናወን የተሳበ ሲሆን በነዚህ ንኡስ ኮሚቴዎች አባላት የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥሪቀርብዋል።

· የተለያዩ የህክምና ጉብኝቶችን ማካሄድ፤ የጥናት እና ምርምር የሚቀርብባቸው መድረኮች ማካሄድ፤ የተለያዩ የሴቶች ጤና ላይ ያተኮሩ የህብረተሰብ ግንኙነት ማካሄድ መታሰባቸውን ገልፀዋል።

· ከጤና ጥበቃ ፤ከተለያዩ አለም እና አገር አቀፍ ተቋማት ጋር የተጀመሩትን ትብብሮች አጠናክሮ መቀጠል፤ በዚህም የለቀ ተሰሚነት እና ተፀእኖ ፈጣሪ የሆነ ማህበር መመስረት እንደታሰበ አስረድተው ሪፖርታቸውን አጠቃለዋል።




የስብሰባው አስተዋዋቂ ዶ/ር ልዕልና ሺመልስ የስራ ሪፖርት ዝርዝር በጥሩ ሁኔታ መቅረቡን ገልፀው አባላቱን ለውይይት ጋብዘዋል፡፡


ውይይት

በውይይቱ ወቅት የተነሱት ዋና ዋና ሀሳቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡

Ø ከስራ ክንውን ሪፖርት ጋር የኦዲት ሪፖርት ቢቀርብ እና ብንወያይበት

Ø የኢትዮጰያ የህግ ሴቶች ባለሙያዎች ማህበር የተደረገለትን ጥሪ በማመስገን ከኢሴሃማ ጋር በጋራ የሴቶችን መብት እና የሙያ ስነ ምግባር ላይ ለመስራት ጥሪ አቅርብዋል።

Ø በህክምና ስህተቶች ሲፈጠሩ የሬታ ሰሚ የህክምና ቦርድ ያለበትን የፍትህ አሰጣጥ ክፍተት የኢሴሃማ በነዚህ ቦርዶች ላይ ያለውን ተሳትፎ ለመጨመር ምን እንደታሰበ ተጠይቅዋል።

Ø የቀድሞ የኢሴሃማ ሊሰራ ከተነሳቸው ውስጥ ሴቶች ላይ ያተኮረ ክሊኒክ አንዱ ነበር በዚህ ረገድ አሁን ያለው የማህበሩ አመራር ከህግ ሴቶች ባለሙያዎች ማህበር ጋር ሊሰራ ያሰበው እቅድ ካለ እንዲጠቀስ ጠይቀዋል።

Ø ብዙ አቅም ያላቸው ሴት ሃኪሞች ስላሉ በዚህ ረገድ ማህበሩ ሊያካሂደው ያሰበው ካለ ቢጠቀስ እንዲሁም የተለያ


በማህበሩ የተሰጠ ምላሽ

Ø የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቱ ያላቸው የፋይናንስ እና አስተዳደር እውቀት ውስን በመሆኑ አማካሪ ቀጥረው ሲያሰሩ የቆዩ መሆናቸውን እና የፋይናንስ ሪፖርቱ ተዘጋጅቶ ያለቀ ቢሆንም የኦዲት ሪፖርት መቅረብ እንዳለበት የተገነዘቡ በመሆናቸው በቀጣይ በሚቀጠሩት ዋና ስራ አስፈፃሚ እና የፋይናንስ ባለሙያዎች ተገቢውን ዝግጅት ተደርጎ በቀጣይ ይህንን የኦዲት ሪፖርት ለጠቅላላ ጉባኤው በማቅረብ እንደ ሚያፀድቅ ተገልፅዋል ።


Ø በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ የህክምና ባለሙያዎች እያደረጉት ላለው እንቅስቃሴ ድጋፍ ለመስጠት እና የተጀመሩ ጉዳዮች አጠናክረው ለመቀጠል እንደሚያስቡ ተገልፀዋል። በተለይ ከኢትዮጰያ የህግ ሴቶች ባለሙያዎች ጋር አብረው ለመስራት ያላቸውን ተነሳሺነት ገልፀው በቀጣይ ከማህበሩ አመራሮች ጋር ተቀምጠው በግልፅ ሊተባበሩባቸው የሚገቡትን አቅጣጫዎች ለመቅረፅ እንደሚሹ ተጠቁሞል።


Ø የህክምና ቦርድ ውስጥ ያለውን ክፍተት የጉዳት ሰለቦች ቶሎ ወደ ጤና ተቋማት መሄድ እንደሚያስፈልጋቸው የግንዛቤ ስራ መስራት ባሻገር በፆታዊ ኦዲት ስራ ውስጥ ማህበሩ የበኩሉን እያካሄደ መሆኑን ተገልፅዋል።


Ø በማህበሩ ሪፖርት ላይ እንደተገለፀው በሴቶች ጤና ላይ ለመስራት የታሰበው ዋና ግብ ውስጥ በውስጡ የተለየ ክሊኒክ አስፈላጊነት ከታመነበት መካተት እንደሚችል እና የመሪነት ስልጠና ለሴት ሃኪሞች ከመስጠት ባሻገር ወንዶችንም ተሳታፊ ማድረግ እንደሚታሰብ ተገልፀዋል።


Ø በሴት ሃኪሞች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃትን ክብደት ማህበሩ በተሳተፈባቸው የተለያዩ የውይይት መድረኮች ላይ መገንዘብ የቻለ መሆኑን እና ሁሉም የማህበሩ አባላት ባሉበት ሁላ ለሴቶች ባጠቃላላይ መብት ጥብቅና እንዲቆሙና በተለያዩ የመሪነት ቦታዎች በፍቃደኝነት በመሳተፍ የሴት ሃኪሞችን ድምፅ ከፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርበዋል።


የስብሰባው አስተዋዋቂ ዶ/ር ልዕልና ሺመልስ በመቀጠል የማህበሩን አርማ የመምረጥ ሂደትን ለማከናወን እና የአባላትን የአመታዊ መዋጮ ለመወሰን ዶ/ር ኤደን ፍስሃን ወደ መድረክ ጋብዘዋል። ከዚህ በተጨማሪ ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት አስመራጭነት ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ ለቤቱ አቅርበዋል። ዶ/ር ማህሌት በኢሴሃማ ስራ አስፈፃሚነት ሊያገለግሉ ስለማይችሉና ባላቸው ልምድ ተሳታፊዎች እንደሚቀበሉት ተጠይቆ በሙሉ አወንታዊ መልስ ፀድቅዋል።


ዶ/ር ኤደን ፍስሃ ማህበሩ እስካሁን ሲጠቀምበት የነበረውን አርማ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ አቅርቦ ለማስወሰን እንደፈለገ እና ይህንን ለማካሄድ ደሞ ሶስት አማራጮች መቅረባቸውን ጠቅሰዋል። አማራጮችንም ከሰዎች ጋር በመቀናጀት የተነደፈ ሲሆን የማህበሩን ስራዎችን የሚያሳዩ ጉዳዮች ትኩረት ያደረገ እንደሆነ አስረድተዋል። በዚህም መሰረት ለአማራጭነት ከቀረቡት ውስጥ በአንዱ ላይ ድምፅ እንዲሰጡ ተጠይቀዋል። አማራጮቹም

1. የመጀመሪያው አርማ EMeWA የሚል ፅሁፍ ሲሆን በመካከሉ የስቴትስኮፕ እና የሴት ምልክት ምስል የሚገኝበት ነው

2. ሁለተኛው አርማ EMeWA የሚል ሲሆን አርማው በአረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ቀለም የተሰራ ነው

3. ሶስተኛው አርማ የኢትዮጰያ ካርታ ላይ ስቴትስኮፕ ያነገበች የሴት ምስል ያካተተ ነው

4. በዚህ መሰረት ከላይ ከተጠቀሱት አርማዎች ውስጥ ተሳታፊዎቹ ሃሳብ እንዲሰጡባቸው ተጠይቅዋል።


ውይይት

በውይይቱ ወቅት የተነሱት ዋና ዋና ሀሳቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡


Ø የቀረቡት አርማዎች ጥሩ ሲሆኑ በተለይ በሶስተኛው ላይ የማህበሩ ስም ፤ የማህበሩ የምስረታ ጊዜ እና የአርማው ስኬል ተስተካክሎ መቅረብ ቢችል

Ø የመጀመሪያው እና ሁለተኛው ላይ ያለውን ፅሁፍ በሶስተኛው ላይ ማካተት ቢቻል


የጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ:

በቀረበው የማህበሩ አርማ አማራጮች ላይ አባላቱ እጅ በማውጣት ድምፅ እንዲሰጡ ከተደረገ በኋላ ድምጹ ተቆጥሮ የሚከተለውን ውጤት ተገልፀዋል።


2. ሁለተኛ አር ማ_______ 0 ድምፅ

3. ሶስተኛ አርማ _______ ሙሉ ድምፅ


በዚህም መሰረት ሶስተኛው አማራጭ አርማ በአብላጫ ድምፅ የማህበሩ አርማ ሆኖ ተመርጥዋል፡፡

Ø ከቀረቡት የአርማ አማራጮች ውስጥ ሶስትተኛውም በአብላጫ ድምፅ የተመረጠ ሲሆን በተሰጠው አስተያየት መሰረት አሻሽሎ ወደ ትግበራ መግባት እንዲቻል ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሀላፊነት በመስጠት አፅድቋል፡፡


ዶ/ር ኤደን ፍስሃ በመቀጠል የማህበሩ አባላት በየአመቱ ሊከፍሉት የሚገባውን የአባላትን የክፍያ መዋጮ መጠን ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እንዲሰጥ ጠቅላላ ጉባኤው ተጠይቅዋል። በዚህም መሰረት ለመደበኛ አባላት አመታዊ ክፍያ ምን ያህል መሆን እንዳለበት ሃሳብ እንዲሰጡ ተሳታፊዎችን ጋብዘዋል።

ውይይት

በውይይቱ ወቅት የተነሱት ዋና ዋና ሀሳቦች የሚከተሉት ናቸው፡፡

Ø ከ500 ብር የበለጠ ቢሆን እና 1000 ብር ባይበልጥ

Ø ከሌሎች ማህበራት አንፃር ታይቶ ከ300 ብር ያላነሰ ከ500 ብር ያልበለጠ ቢሆን እና በቅድሚያ አባላትን መሰብስብ ተቀዳሚ ትኩረት ቢሆን

Ø ከልምድ ደግሞ የተባባሪ አባላት ከመደበኛ አባላት ክፍያ ግማሽ ቢሆን

Ø አባል መሆን ሊያስገኝ የሚችለውን ጥቅም ቢጠቀስ ለውሳኔ ይረዳል


የጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ:

በቀረበው የመደበኛ አባል አመታዊ የመዋጮ ክፍያ ብር 1000፣ 500 እና 300 አማራጮች ላይ አባላቱ እጅ በማውጣት ድምፅ እንዲሰጡ ከተደረገ በኋላ ድምጹ ተቆጥሮ የሚከተለውን ውጤት ተገልፀዋል።

2. 300 ብር _______ 10 ድምፅ

3. 500 ብር _______ 23 ድምፅ

በዚህም መሰረት 500 ብር በአብላጫ የመደበኛ አባላት አመታዊ መዋጮ ሆኖ ተወስንዋል፡፡


ዶ/ር ኤደን ፍስሃ በመቀጠል የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን ለማስመረጥ ዶ/ር ማህሌት ይገረሙን እና ዶ/ር ቤቴል ደረጄ ወደ መድረክ ጋብዘዋል።


ከምርጫው መካሄድ በፊት የስፖንሰር ማስታወቂያ ተነግርዋል።

ውይይት

የምርጫ ሂደቱን ለመምራት አስመራጮች መድረኩን ከተረከቡ በሁዋላ ለአባላቱ የምርጫ ሂደቱ ላይ ሃሳብ እንዲያቀርቡ በቅድሚያ እድል ሰጥተዋል በዚህም የተነሱት ዋና ዋና ሃሳቦች የሚከተሉት ናቸው፡


Ø ከነባር የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ውስጥ መቀጠል የሚፈልግ ሊኖር ስለሚችል ከ1/3 በላይ ቢፈቀድ

Ø የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የነበረበት ክፍተት ስለነበረው በአዲስ አመራር ቢለወጥ እና ነባር ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ግን በተለያዩ ኮሚቴዎች ተሳትፎውያዋቸውም ቢቀጥሉ

Ø በተለያዩ የምርጫ ስርአቶች እንደምናየው ነባር የስራ አስፈፃሚዎችም ይሁኑ አዲስ እጩዎች ከጥቆማ ይልቅ እራሳቸውን በእጩነት ካቀረቡ በሁዋላ ምን መስራት እንደሚፈልጉ እና ለምን መመረጥ እንዳለባቸው ለአባላቱ ቅስቀሳ ቢያደርጉ እና ከዚህ ተነስቶ ጠቅላላ ጉባኤው ቢመርጥ


በዚህም መሰረት አስመራጮቹ በተሰብሳቢዎቹ ውስጥ በተነሱት ሃሳቦች መሰረት አድርገው ሶስት አካሄዶችን ለቤቱ ምርጫ አቅርበዋል። በእነዚህ ላይ ቤቱ እጅ በማውጣት ድምፅ እንዲሰጡ ጠይቀዋል። የቀረቡት የምርጫ አካሄዶች የሚከተሉት ናቸው፤


1. አዲስ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን እንምረጥ

2. የነበረው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በነበረበት ይቀጥል

3. ከነበሩት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ውስጥ መቀጠል የሚፈልጉት በግልፅ በድጋሚ መመረጥ እንደሚፈልጉ እና ለምን መመረጥ እንዳለባቸው እንዲያብራሩ ከዛም ቤቱ በጎደለው ላይ ምርጫ ያካሂድ


የጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ:

አስመራጮቹ ከቀረቡት አማራጮች ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ሶስተኛውን አካሄድ ማፅድቁን ገልፀዋል።


ከዚህ በመቀጠል ነባር የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ወደ መድረክ ወጥተው እራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ፤ መቀጠል እንደሚፈልጉ እና እንደማይፈልጉ፤ ከፈለጉ ደግሞ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ በምን ሃላፊነት እና ምን ለመስራት እንደሚያስቡ እንዲገልፁ ጋብዘዋል።

ወደ መድረክ በመውጣት ነባር የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቱ አጭር ንግግር አድርገዋል። በዚህ መሰረት የሚከተለውን ገለፃ አባላቱ ሰጥትዋል


1. ዶ/ር ሃማኖት የየሱስወርቅ(የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ግዚያዊ ፕሬዚዳንት)የተጀመረውን የማህበሩን ጉዞ በማስቀጠል የሚመጣውን አመራር ለመደገፍ ያላቸውን ፍላጎት ገልፀው በስራ አስፈፃሚ አባልነት ብቻ ለመቀጠል እንደሚሹ ተናግረዋል።

2. ዶ/ር ቃልኪዳን አላቸው(የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል)በኮሚቴው አባልነት መቀጠል ቢፈልጉም ከሳቸው የተሻለ ልምድ እና ችሎታ ላላቸው አባላት እድሉን መስጠት አስፈላጊ ነው ብለው ስለሚያምኑ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴነት መቀጠል እንደማይፈልጉ ተናግረዋል። ሆኖም በልዩ ኮሚቴዎች ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል።

3. ዶ/ር ሙና አብዱልቃድር (የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል)ከሳቸው የተሻለ ልምድ እና ችሎታ ላላቸው አባላት እድል ለመስጠት በስራ አስፈፃሚነት ኮሚቴነት መቀጠል እንደማይፈልጉ ተናግረዋል።

4. ዶ/ር ፍረወይኒ አባይ (የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የፋይናንስ ተጠሪ) ለማህበሩ በተለያዩ ደረጃዎች ያገለገሉ እንደሆነና፤ ምንም እንኩዋን የፋይናንስ እውቀት ባይኖራቸውም በስራ አስፈፃሚነት አባልነት ብቻ ለመቀጠል እንደሚሹ ተናግረዋል።

5. ዶ/ር ነቢያት ሰመረዲን(የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል)ማህበሩ ውስጥ ብዙ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ቢችሉም ባለባቸው የስራ ጫና እና የተሻለ ልምድ እና ችሎታ ላላቸው አባላት እድል ለመስጠት በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴነት መቀጠል እንደማይፈልጉ ተናግረዋል። ሆኖም በልዩ ኮሚቴዎች ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል።

6. ዶ/ር ኤደን ፍስሃ (የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል)ማህበሩ ውስጥ ብዙ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ቢሞክሩም ያሰቡትን ያክል እንቅስቃሴ ስላልነበራቸው በስራ አስፈፃሚነት ኮሚቴነት መቀጠል እንደማይፈልጉ ተናግረዋል። ሆኖም በልዩ ኮሚቴዎች ውስጥ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል።

7. ዶ/ር ቤቴል ደረጄ (የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ም/ፕሬዚዳንት)ማህበሩ ውስጥ ብዙ ተሳትፎ ያደረጉ ቢሆንም በአሁኑ ሰአት ባለባቸው የስራ ጫና እና የተሻለ ልምድ እና ችሎታ ላላቸው አባላት እድል ለመስጠት በስራ አስፈፃሚነት ኮሚቴነት መቀጠል እንደማይፈልጉ ተናግረዋል። ሆኖም በልዩ ኮሚቴዎች ውስጥ በመሪነት ላይ በሚደረጉት ስልጠናዎች ላይ የበኩላቸውን ለማበርከት እንደሚፈልጉ እና ቃል እንደሚገቡ ገልፀዋል።

8. ዶ/ር ሊዲያ ተፈራ (የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል)ማህበሩን ለማገልገል ፍላጎት ቢኖራቸውም ካላቸው የስራ መደራረብ ለማህበሩ በቂ ጊዜ ላይሰጡ ስለሚችሉ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴነት መቀጠል እንደማይፈልጉ ተናግረዋል። ከዚህ ጋር አያይዘው ማህበሩን ሲያገለግሉ የነበሩትን ዶ/ር ሰናይት እና ዶ/ር ልዕልናን ለምርጫው እንደሚጠቁሙ ገልፀዋል።


አስመራጮቹ መድረኩን በመረከብ የስራ አስፈፃሚ አባላቱን መልስ አጠቃለው ይፋ አድርገዋል። በዚህ መሰረት ከዘጠኝ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ውስጥ ስምንቱ እንደተገኙ ፤ በስብሰባው ዶ/ር ኢትዮጵያ ቁምላቸው እንደሌሉና በዚህ መሰረት ከዘጠኙ ሁለቱ ብቻ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት መቀጠል እንደሚፈልጉ አስገንዝበዋል። በመቀጠልም የምርጫው አካሄድ የሚሆነው ለሰባት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት ዘጠኝ ሰው ጠቅላላ ጉባኤው እንደሚጠቁም ከዛም ውስጥ ለአራቱ የስራ ሃላፊነቶች እጩዎች እንደሚወዳደሩ አስረድተዋል።

አስመራጮቹም ከስብሰባው ተሳታፊዎች ውስጥ በድጋሚ ተጨማሪ ሃሳብ አስተናግዋል።




ውይይት

የሚከተሉት ሁለት ሃሳቦች ከተሳታፊዎች ቀርበዋል


Ø የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላቱ እንደተናገሩት በስብሰባው ውስጥ ያሉ ተሳታፊዎች ደግሞ እድል ተሰጥትዋቸው እራሳቸውን በማስተዋወቅ በሚቀጥለው ሁለት አመት ውስጥ ይህን መስራት እፈልጋለሁ፤ ይህን ለማሳካት ፍላጎት አለኝ የሚሉ የማህበሩ አባላት የምረጡኝ ቅስቀሳ ማድረግ እንደአካሄድ እንዲፈቀድ ሃሳብ አቅርበዋል።

Ø በተጨማሪም እራሳቸውን ለውድድሩ የሚያጩ ሰዎች አቅም ላይ ብቻ ሳያተኩሩ የሚወዱትን እና ሊሰሩ ያሰቡትን በመግለፅ ያለባቸውን ጉድለት በተለያዩ መንገዶች ሊገነቡት ስለሚችሉ በራስ በመተማመን እራሳቸውን እንዲያስተዋውቁ ጥሪ ቀርብዋል።


የጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ:

ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ የስብሰባው ተሳታፊዎች እያነሱት ያለው ሃሳብ እጅግ አስደሳች እና ታሪካዊ መሆኑን ገልፀው ይህንን አካሄድ ጠቅላላ ጉባኤው እንደሚደግፈው ከጠየቁ በሁዋላ ተሳታፊዎች መስማማታቸውን ገልፀዋል። እንደ አካሄድም ተሳታፊዎቹ በተቀመጡበት መደዳ መሰረት በመነሳት ለስራ አስፈፃሚነት መወዳደር ለምን እንደሚፈልጉ እና በየትኛው የሃላፊነት መደብ ላይ መሳተፍ እንደሚፈልጉ እንዲገልፁ እድሉን ሰጥተዋል። በዚህ መሰረት አባላቱ የሚከተለውን የምረጡኝ አጭር ንግግር አድርገዋል።


1. ዶ/ር አዜብ አሳምነው በደብረማርቆስ ሪፈራል ሆስፒታል ሳይኪያትሪስት እንደሆኑ ከገለፁ በሁዋላ በተደረገው የቤቱ የአካሄድ ለውጥ እንደተደሰቱ በመግለፅ ንግግራቸውን ጀምረዋል። በመቀጠልም ኢሴሃማ ሲቆቆም በቦታው ባለመኖራቸው እንጂ ሊሰርዋቸው ከሚፈልግዋቸው ውስጥ እንደሆነ እና ይህን ለማድረግ ደግሞ አሁን ያለው መድረክ ከተመቻቸ በስራ አስፈፃሚነት ማገልገል እንደሚፈልጉ አስታውቀዋል። ልምዳቸውንም ሲያብራሩ፤ በኢትዮጵያ የህክምና ተማሪዎች ማህበር ውስጥ መስራች እና በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ በተለያዩ ሃላፊነቶች ላይ ያገለገሉ መሆኑን ጠቁመዋል። በ2018 የማንዴላ ፌሎ የነበሩ ሲሆን አሁን ደግሞ በበጎ ፈቃደኝነት በማንዴላ ኢትዮጵያን ዶክተርስ የተባለው ውስጥ ከኢሴሃማ ጋር በመሆን የፆታዊ ጥቃት በህክምና ባለሙያዎች ላይ በሚል ርዕስ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል። ያላቸውን በሴቶች መብት ላይ የመስራት ፍላጎት የኢሴሃማ አመራር አባል በመሆን ማህበሩ ያለውን ተሰሚነት በመጠቀም የተሻለ ስራ ለመስራት እድል እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል። ምንም እንኩዋን ካሉበት የቦታ እርቀት አንፃር በሁሉም ስብሰባ ላይ መገኝት ሊከብዳቸው ቢችልም በኦንላይን እንዲሁም በስልክ በቀላሉ መሳተፍ እንደሚችሉ እና ካላቸው የሰዎች ግንኙነት አንፃር ለማህበሩ አስተዋፀኦ ለማበርከት እንደሚሹ እንዲሁም ከፕሬዚዳንት እና ም/ፕሬዚዳንትነት ቦታዎች ውጪ በማህበሩ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ ቢሰሩ ደስ እንደሚላቸው ገፀዋል።

2. ዶ/ር ሰላማዊት እሸቱ በፌዴራል ፖሊስ ሆስፒታል ጠቅላላ ሃኪም እንደሆኑና በአሁኑ ሰአት በPublic health nutrition እየተማሩ እንደሆነ በከገለፁ በሁዋላ በ’Nutrition for education development ‘ በሚል ፕሮግራም ላይ በበጎ ፈቃደኝነት እያገለገሉ መሆኑን ገልፀዋል። የተለየ የመፃፍ እና እንቅስቃሴዎችን የመምራት ችሎታ ስላላቸው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ቢሆኑ ይህን ችሎታቸውን በመጠቀም ሊያገለግሉ እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።

3. ዶ/ር አቦነሽ እሸቱ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ኢንተርን እንደሆኑ ገልፀው ከህክምና ትምህርታቸው በፊትም በሚኖሩበት አካባቢ ይሁን አሁን ባሉበት ሆስፒታል ውስጥ በሴቶች ላይ ይሰሩ እንደነበረ እና በተለይ በህክምና ት/ቤት ውስጥ በተማሪዎች ካውንስል፤ በሴቶች ጉዳይ እና ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች በስራ አስፈፃሚነት በመሳተፍ ላይ ንቁ ተሳትፎ ያደርጉ እንደነበር ገልፀዋል። የኢሴሃማ መቋቋም ሲረዱ ይህን እድል ሲፈልጉት እንደነበረ እና በዚህ ስብሰባም መገኘታቸው እንዳስደሰታቸው ገልፀው በማህበሩ የቀረቡት ሃሳቦች ላይ ለመስራት እንደሚፈልጉ እና በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት ይህንን ለማከናወን እድል እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል። አስቸጋሪ ሊሆን የሚችለው ከህክምና ትምህርታቸው ከተመረቁ በኋዋላ የት ሊመደቡ እንደሚችሉ የማያውቁ ቢሆንም ያላቸውን ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት በሚሄዱበት አካባቢ የማህበሩን ስራ እና በሴቶች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ በመቀጠል መሳተፍ እንደሚፈልጉ ከገለፁ በሁዋላ እንደወጣት የህክምና ተማሪነታቸው ከሲኒየር መምህራን ጋር የመስራት ልምድ ያላቸው በመሆኑ ማህበሩን ማገልገል እንደሚሹ ገልፀዋል።


በነዚህ ንግግሮች መሃል ከተሰብሳቢዎቹ ውስጥ አስተያየት መስጠት የሚሹ ግለሰቦች ስለነበሩ ዶ/ር ማህሌት እድል ሰጥተዋል። በዚህም የተነሱት ሃሳቦች


Ø እጩዎች የሚወዱትን ብቻ ሳይሆን የሚችሉትን እና ብቃት ያላቸውን ነገር ለመስራት እንዲነሳሱ ጥሪ ቀርብዋል

Ø ከአዲስ አበባ ውጪ የሚኖሩ እጩዎች በሁሉም ስብሰባ ላይ ተሳታፊ መሆን ስላለባቸው እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መሆን ደግሞ ሃላፊነት ስለሆነ በተቻለ መጠን እጩዎች ይህንን ታሳቢ ቢያደርጉ

Ø የማወዳደሪያ መስፈርቶች በህገ ደንቡ እንዲሁም በጠቅላላ ጉባኤው መወሰኑ ስለማይቀር እጩዎች ንግግራቸውን እንዲቀጥሉ እና ከላይ የተነሱትን ሃሳቦች ከግንዛቤ ቢያስገባ


ከላይ የተሰጡትን ሃሳቦች መድረኩ ተቀብሎ በድጋሚ እጩዎች እራሳቸውን የማስተዋወቅ ሂደቱ ቀጥልዋል።

4. ዶ/ር ትግስት አስቻላቸው የህፃናት ሃኪም ሲሆኑ በአሁኑ ሰአት በግል ሆስፒታል እየሰሩ ሲሆን ማህበሩ የሚሰጣቸውን ሃላፊነት ለመወጣት ዘግጁ እንደሆኑ እና በተለይ በስራ አስፈፃሚነት ቢመረጡ እንደ ማህበሩ አባል፤ ሴት ሃኪም፤ እና ሃገር የድርሻቸውን ለመወጣት እንደሚፈልጉ እና እድሉ ከተሰጣቸው ይህንን ለማድረግ እንደሚሹ ገልፀዋል።

5. ዶ/ር ሰናይት በየነ በአሁኑ ወቅት በጤና ጥበቃ ውስጥ እንደሚሰሩ እና ከዚህ ቀደም የስራ አስፈፃሚ ባይሆኑም ከአባላቱ ጋር በቅርበት ሲሰሩ የነበረ እንደሆነ እና ብዙ ያቀዱዋቸው ነገሮች እንዳሉ እንዲሁም እነዚህን ሃሳቦች ከግብ ማድረስ እንደሚፈልጉ ገልፀዋል። አዳዲስ እና ጠንካራ አባላትን ወደ ማህበሩ ማምጣት እንደሚገባ እና ብዙ የታቀዱ ስራዎችን በአዲስ ጉልበት መስራት እንደሚያስቡ አስገንዝበዋል። የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆነው ቢመረጡ ያላቸውን የስራ ግንኙነቶች በመጠቀም ማህበሩን በተሻለ መልኩ እንደሚያገለግሉ ተናግረዋል።

6. ዶ/ር ቤቴልሄም ———— በአይደር ሪፈራል ሆስፒታል ኢንተር ሲሆኑ የትምህርት ቤታቸው የሴት ሃኪሞችን በማስተባበር እና ማህበራቸውን በማቋቋም ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረጉ ሲሆን፤ ምንም እንክዋን ለጊዜው በመቀሌ የሚገኙ እንደሆነ እና ከተመረቁ በሁዋላ የት ሊሰሩ እንደሚችሉ ባያውቁም፤ ካላቸው ልምድ እና ተሰዛሽነት እድሉ ከተሰጣቸው ማህበሩን ለማገልገል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

7. ዶ/ር ሊድያ ተፈራ ከዚህ ቀደም በስራ አስፈፃሚነት መቀጠል እንደማይፈልጉ የጠቀሱት በስራ መደራረብ ቢሆንም ይህንን ችግር በስራ አካሄድ ሊስተካከል ከቻለ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ውስጥ ማገልገል እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።


በእነዚህ ንግግሮች መሃል ከተሰብሳቢዎቹ ውስጥ አስተያየት መስጠት የሚሹ ግለሰቦች ስለነበሩ ዶ/ር ማህሌት እድል ሰጥተዋል። በዚህም የተነሱት ሃሳቦች

Ø ከዚህ ቀደም ማህበሩ ሊያጋጥመው የሚችላቸውን ክፍተቶች ለመሙላት የስብሰባው ተሳታፊ ሁለት ሃሳቦችን በተጨማሪ አቅርበዋል። በመጀመሪያ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጪ ያሉ ፍቃደኛ እጩዎች በሚገኙበት አካባቢ የኢሴሃማ ተጠሪ መሆን ቢችሉ፤ በመቀጠል ደግሞ ከስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ውስጥ የስራ ዘመን ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ በተለያየ ምክንያት ለሚያቆርጡ ግለሰቦች ሁለት ተጠባባቂ አባላት በዚህ ወቅት አብሮ ቢመረጡ የሚል ሃሳብ ቀርብዋል።


ከላይ የተሰጡትን ሃሳቦች መድረኩ ተቀብሎ በድጋሚ እጩዎች እራሳቸውን የማስተዋወቅ ሂደቱ ቀጥልዋል።

8. ዶ/ር ሜሮን ከበደ ኢንተርን እንደሆኑ ገልፀው በሴቶች ጉዳይ ላይ የስራ አስፈፃሚ አባል ሆነው ማገልገል እንደሚፈልጉ እና ገና የህክምና ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉትን በማሳተፍ በበጎ ፈቃደኝነት መስራት እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።

9. ዶ/ር ቤዛዊት ________ በቅዱስ ፓውሎስ የህክምና ኮሌጅ ኢንተርን ሲሆኑ ከዚህ ቀደም በአመራር ላይ ተሳትፈው ባያውቁም ለሴቶች መብት እና በህክምና ትምህርት ቤት ውስጥ በተለያዩ የሴቶች ፍላጎቶች ላይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ ጉዳዮች እንዳሉ እንደሚያምኑ እና በእነዚህ ዙሪያ በጋር መስራት እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።

10. ዶ/ር ቃልኪዳን ካሳዬ በጀነራል ፕራክቲሽነርነት ከዚህ ቀደም በደብረማርቆስ ሆስፒታል ያገለገሉ ሲሆን አሁን ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን ተናግረዋል። ምንም እንኩዋን ብዙ የአመራር ልምድ ባይኖራቸውም የሚሰጣቸው ሃላፊነት በቁርጠኝነት ለማገልገል እንደሚችሉ እና በተለይ በሴቶች እኩልነት ላይ መስራት እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።

11. ዶ/ር ሃምሌት —————— እዚህ በመገኘታቸውና ይህን እድል ስለተሰጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው በጡርነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል እንደሚሰሩ እና ከዚህ ቀደም በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ውስጥ ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን በሴቶች መብት ላይ እና ማብቃት ላይ የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው እና ማህበሩን በቁርጠኝነት ማገልገል እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።

12. ዶ/ር ቃልኪዳን አላቸው ከዚህ ቀደም በስራ አስፈፃሚነት ለመቀጠል ያገዳቸው ሊኖራቸው የሚችለውን የልምድ ክፍተት አይተው ቢሆንም አሁን አባላቱ ባሰሙት ንግግር ማህበሩን የማገልገል ፍላጎታቸው እንደተነሳሳ ገልፀዋል። ስለዚህም በድጋሚ በስራ አስፈፃሚነት ለመስራት እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።

13. ዶ/ር ነቢያት ሰመረዲን በስራ አስፈፃሚነት መቀጠል እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።

14. ዶ/ር መሪየም ዲኖ በቤቴል ሜዲካል ኮሌጅ ኢንተርን ሲሆኑ የኒውትሪኒሽት በለሙያ መሆናቸውን ገልፀው የተማሪዎች ድምፅ መሰማት እንዳለበት እና ከግል የህክምና ትምህርት ቤት የሚመጡትን ባለዉያዎች መወከል እንዳለባቸው እንደሚያምኑ ገልፀዋል።

15. ዶ/ር ኤደን ፍስሃ ከግል የህክምና ትምህርት ተቆማት የተወከሉ የማህበሩ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት እንዳሉ ገልፀዋል። በተጨማሪ እሳቸውም ማህበሩን ማገልገል መቀጠል እንደሚፈልጉ ገልፀዋል።


ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ በመቀጠል የኢሴሃማ የመተዳደሪያን ደንብ ጠቅሰው በስራ አስፈፃሚነት መመረጥ የሚችሉት ሙሉ አባል የሆኑ ሲሆን ይህም ማለት ከታወቀ የህክምና ትምህርት ተቋም የተመረቀ ማለት እንደሆነ ገልፀው አንተርኖች የተባባሪ አላት ስለሆኑ በተጠባባቂ እጩነት እንደሚያዙ አስረድተዋል። በመሆኑም በህገደንቡ መሰረት ይህን የሚያሙዋሉ ዘጠኝ እጩዎችን አስታውቀዋል። ዶ/ር ሃይማኖት የየሱስወርቅ እና ዶ/ር ፍረወይኒ አባይ በስራ አስፈፃሚነት በበጎ ፈቃደኝነት መቀጠል እንደሚፈልጉ ስላስታወቁ ጠቅላላ ጉባኤው ከቀረቡት እጩዎች ሰባት አባላትን ብቻ እንዲመርጡ አስታውቀው ይህ ከተጠናቀቀ በሁዋላ ለተለያዩት የስራ አስፈፃሚነት ቦታዎች በድጋሚ ምርጫ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል። በዚህ መሰረት የሚከተሉት እጩዎች ለስራ አስፈፃሚነት ቀርበው

1. ዶ/ር አዜብ

2. ዶ/ር ሰላማዊት

3. ዶ/ር ትግስት

4. ዶ/ር ሰናይት በየነ

5. ዶ/ር ቃልኪዳን ካሳዬ

6. ዶ/ር ሃምሌት

7. ዶ/ር ሊዲያ ተፈራ

8 ዶ/ር ቃልኪዳን

8. ዶ/ር ነቢያት

10. ዶ/ር ኤደን


ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ የመራጮች ስም በግልፅ እንዲታይ በኮፒዩተር እስኪፃፍ ድረስ ለተሳታፊዎች እድል ሰጥተዋል።


Ø በተሰጠው የኢንተርኖች ጥያቄ ላይ መሰረት በማድረግ አባላቱን በተለየ የተማሪዎች አባልነት ማሳተፍ ቢቻል

Ø የኢንተርኖች የተለየ ኮሚቴ ቢቋቋም የሚሉ ሃሳቦች ቀርብዋል።


ዶ/ር ማህሌትም የመጀመሪያው ሃሳብ የህገደንብ ለውጥ እንደሆነ እና የዛሬው አጀንዳ ባለመሆኑ ሊካተት እንደማይችል ገልፀው አባላቱ ምንም እንክዋን የስራ አስፈፃሚ አባል መሆን ቢችሉም ድምፅ መስጠት እንደማይችሉ ገልፀዋል። ነገርግን የቀረቡትን አምስት ኢንተርን እጩዎች በተለየው የኢንተርን ዌልፌር ኮሚቴ አባልነት በቀጥታ እንዲመረጡ ጠቅላላ ጉባኤውን ጠይቀዋል። በዚህ መሰረት እጩዎቹ

1. ዶ/ር አቦነሽ

2. ዶ/ር ቤቴልሄም

3. ዶ/ር ሜሮን ከበደ

4. ዶ/ር ቤዛዊት

5. ዶ/ር መሪየም


ጠቅላላ ጉባኤውም በሙሉ ድምፅ ለሁለት አመት ጊዜ ለኢንተርን ዌልፌር ኮሚቴነት አባልነታቸውን አፅድቅዋል።

በመቀጠል እጩዎቹ ወደመድረክ በመውጣት በደረታቸው ላይ ስማቸውን በግልፅ ከፃፉ በሁዋላ ጠቅላላ ጉባኤው በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ ሰባት ምርጫቸውን የእጩዎች ስም በወረቀት እንዲያሰፍሩ ዶ/ር ማህሌት ይገረሙ ጠይቅዋል። በመቀጠልም ይህ ታሪካዊ ቀን እደሆነ ገልፀው የምርጫ ስርአቱ ለሌሎች ማሳያ እንደሆነ ገልፀዋል። የተሰብሳቢዎቹን ወረቀት ፍቃደኛ የሆኑትም አባላት እንዲሰበስቡ እና ወደ ቆጠራው እንዲገባ ጠይቀው እጩዎችንም ወድ ቦታቸው በክብር ሸኝተዋል።

የስብሰባው መሪ ዶ/ር ልዕልና በመቀጠልም ለተሰብሳሚዎቹ የምርጫ ሂደቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ከኢትዮጰያ ነርሶች ማህበር እንግዳ ሃሳባቸውን እንዲያካፍሉ እድሉን ሰጥታቸዋለች።


Ø የኢትዮጵያ ነርሶች ማህበር ተወካይ የሆኑት እንግዳ ማህበሩን ጥሪ ስላደረገላቸው በማመስገን እና የስብሰባው ተካፋይ መሆናቸው እንዳስደሰታቸው በመግለፅ ንግግራቸውን ጀምረዋል። የነበረውን የእስካሁኑ ቆይታ አስደሳችነት ገልፀው በተለይ በሴቶች ላይ ስለሚደርሰው ፆታዊ ጥቃት ምን መደረግ እንዳለበት እና እንዴት ሁለቱ የሙያ ዘርፎች በጋራ መስራት እንዳለባቸው ገልፀዋል። ሴቶች በአንድ ላይ ለመስራት የሚያስችል ቁጥር እና ግንኙነት ስላላቸው በስራ ላይ ተዋዶ እና ተከባብሮ መኖር አስፈላጊ እንደሆነ እና ሴቶች ላይ ያለውን ጥቃት በጋራ መስራት የሚችሉበትን መንገድ ለማምጣት እንደ የማህበራቸው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል። ከውስጣዊ የስራ ባለሙያዎች ችግሮች መውጣት እና የፀዳ መሆን ከተቻለ ከማንኛውም የፆታዊ ጥቃት በስራም በኢትዮጵያም ደረጃ ይመጣል ብለው እንደሚያምኑ እና በይበልጥ ያላቸውን አቅም በጋራ ለመስራት የሚቻልበትን መንገድ ማህበሩ እንዲያስብበት ጠይቀዋል። የማህበሩን የቀድሞ እና መጪ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትን እንኳን ደስ ያለን ያሉ ሲሆን በቅብብል አመራሩ እንዲሰራ አደራ ካሉ በኋዋላ በአሁኑ ሰአዕት የሚሰሩት በሃምሌ ፌስቱላ እንደሆነ እና በስብሰባው የሚገኙትን ሴት ሃኪሞች በማእከላቸው ተገኝተው የጥቃቱን ተጎጂዎች ለመርዳት በበጎ ፈቃደኝነት ምን እንስራ ብለው እንዲጠይቁ ጥሪ አቅርበዋል።


Ø እስከአሁን በተደረገው ውይይት ስለ ፆታዊ ጥቃት ብዙ ተነስቷል፡፡ ነገር ግን እንደ አዲስ ተመራቂ ያልታዩ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ አብዛኛው ተመራቂ ተመርቆ ወዲያው ስራ የሚያገኝ ይመስለዋል አሁን ባለው ሁኔታ ግን ለስራ ቅጥር የሚጠየቁ ጥያቄዎች አሉ፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ከስራው ጋር ግንኙነት የሌላቸው የግል ጉዳዮች ሲሆኑ ሴት በመሆናችን ብቻ ወደ ኋላ የሚጎትቱ ናቸው፡፡ ይሀ ጉዳይ በማህበሩ በምን መልኩ እንደሚታይ ቢገልፅ

Ø ማህበሩን ከአመራርነት ውጪ ልናገለግልበት የምንችልበት አማራጭ ካለ ቢነገር


ምላሽ

ዶ/ር ሃይማኖት ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ፤ የተነሳው ሀሳብ ትክክል መሆኑን እና በተጨባጭ እየታየ ያለ ችግር ስለሆነ በጉዳዩ ላይ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በስራ ቅጥር ወቅት ብቻ ሳይሆን በህክምና ስራ ወቅትም ፈተናው ብዙ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ የተቀመጠ ህግ ባይኖርም በአስተዳደራዊ ጫና ምክንያት የተለያዩ በደሎች እየደረሱ ነው ብለዋል፡፡ የማህበሩ አላማም እነዚህን ጉዳዮች ላይ ጠንከር ያለ አቋም ወስዶ ለመብታችን በመታገል ለውጥ ማምጣት ነው ፡፡ በአንድነት መቆም ተደማጭነትን ያስገኝልናል በማለት አባላት ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

በመቀጠልም የአስመራጭ ኮሚቴ አባል የሆኑት ዶ/ር ቤቴል የተደረገው ምርጫ ውጤት ይፋ አድርገዋል፡፡ በዚህም መሰረት

1. ዶ/ር ሊዲያ ተፈራ - 38

2. ዶ/ር ቃልኪዳን አላቸው - 36

3. ዶ/ር ሰላማዊት - 32

4. ዶ/ር ሰናይት - 29

5. ዶ/ር ኤደን - 28

6. ዶ/ር አዜብ - 27

7. ዶ/ር ነቢያት - 23

8. ዶ/ር ትእግስት - 22

9. ዶ/ር ቃልኪዳን አሳዬ - 21

10. ዶ/ር ሀምሌት - 12 አግኝተዋል፡፡

ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያ 7 ትልቅ ውጤት ያመጡት በቀጥታ ሲመረጡ 2 በፈቃደኝነት ከቀጠሉት ጋር 9 አባላት ያሉት ኮሚቴ ሆነዋል፡፡ ከ9 ተመራጮች ውስጥ ለፕሬዘዳንትነት፣ ለም/ፕሬዘዳንትነት፣ ለሴክረታሪ እና ለፋይናንስ ምርጫ እንደሚካሄድ አሳውቀዋል፡፡ በቅድሚያ ግን ራሳቸውን በፈቃደኝነት ለሚያጩ ሰዎች እድል ተሰጥቷል፡

1. ዶ/ር ሊዲያ ተፈራ: ከዚህ ቀደም ሴክረታሪ ሆነው ስለሰሩ በአሁኑ ም/ፕሬዝዳንት ለመሆን ራሳቸውን አጭተዋል፡፡ በቂ ሰዐት ስለሚኖራቸውም በትጋት እንደሚያገለግሉ ተናግረዋል፡፡

2. ዶ/ር ቃልኪዳን አላቸው: ከዶ/ር ሊያዲ ያገኙትን ልምድ በመጠቀም ለማገልገል ሴክረታሪ ለመሆን እንደሚፈልጉ ገልፀዋል፡፡

3. ዶ/ር ሰላማዊት እሸቱ: በአመራርነት ልምድ ስሌላቸው ም/ፕሬዝዳንት ሆነው ማገልገል እንደሚመርጡ ሀሳብ ሰተዋል፡፡

4. ዶ/ር ሰናይት በየነ: ፕሬዝዳንት መሆን እንደሚችሉ ገልፀዋል፡፡

5. ዶ/ር ኤደን ፍሰሃ: በፊት በነበሩበት የኮሚቴ አባልነት ብቻ መቀጠል እንደሚልጉ ተናግረዋል፡፡

6. ዶ/ር አዜብ አሳምነው: ከሚሰሩበት ቦታ ርቀት አንፃር አባል መሆንን መርጠዋል፡፡

7. ዶ/ር ነቢያትሰምረዲን: በአባልነት ለማገልግል ፍላጎታቸውን አስረድተዋል፡፡

8. ዶ/ር ፍረወይኒ አባይ: ለፕሬዝዳንትነት ራሳቸውን አጭተዋል፡፡

9. ዶ/ር ሀይማኖት የየሱስወርቅ: በፕሬዝዳንትነት ባገለገሉበት ጊዜያት ከስራ ጋር ከፍተኛ ጫና ስለፈጠረባቸው አባል ብቻ ሆነው መቀጠል እንሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡


አስተያየት

በፋይናንስ ዘርፍ የታጫ/ያጨ ባለመኖሩ ጉባኤው የራሱን ድምፅ እንዲሰጥ ተጠይቋል በተጨማሪም የፋይናንስ የስራ ድርሻ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡


በመቀጠልም የድምፅ አሰጣጡ ተጀምሯል፡፡ በተደረገውም ምርጫ መሰረት

1. ዶ/ር ቃልኪዳን - 41 ድምፅ- ፕሬዝዳንት

2. ዶ/ር ሰናይት - 38 ድምፅ - ም/ፕሬዝዳንት

3. ዶ/ር ሊዲያ - 37 ድምፅ - ሴክረታሪ

4. ዶ/ር ፍረወይኒ - 26 ድምፅ - ፋይናንስ በመሆን አሸንፏል፡፡


በምርጫው አካሄድ ላይ በተፈጠረ የሀሳብ ልዩነት ድምፅ አሰጣጡ ላይ ለውጥ በመምጣቱ በድምፅ ቆጠራው ላይ ማሻሻያ ተደርጎ በድጋሚ ለማየት ተወስኖ ጉባኤው ለምሳ ወጥተዋል፡፡


ከ7፤00 እስከ 8፤00 ሰ ድረስ ጉባኤው ለምሳ እረፈት ተቋረጠ፡፡



ከምሳ መልስ የአስመራጭ ኮሚቴው የድምፅ ቆጠራ ሂደቱን ካብራሩ በኋላ ውጤቱን እንደሚከተለው ገልፀዋል፡፡

· ለፕሬዚዳንትነት ከታጩት

o ዶ/ር ቃልኪዳን - 1 ድምፅ

o ዶ/ርሰናይት - 25 ድምፅ

o ዶ/ር ፍረወይኒ - 15 ድምፅ አግኝተዋል፡

በዚህም መሰረት ዶ/ር ሰናይት በአብላጫ ድምፅ ፕሬዚዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡


· ለም/ፕሬዝዳንት ከታጩት

o ዶ/ር ቃልኪዳን - 1 ድምፅ

o ዶ/ርሰናይት - 2 ድምፅ

o ዶ/ር ሊዲያ - 39 ድምፅ

o ዶ/ር ሰላማዊት - 2 ድምፅ

o ዶ/ር ፍረወይኒ - 3 ድምፅ አግኝተዋል፡፡

በዚህም መሰረት ዶ/ር ሊዲያ ተፈራ በአብላጫ ድምፅ ም/ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል፡፡


· ለሴክረታሪ ከታጩት

o ዶ/ር ቃልኪዳን - 38 ድምፅ

o ዶ/ር ሰናይት - 1 ድምፅ

o ዶ/ር አዜብ - 1 ድምፅ አግኝተዋል፡፡

በዚህም መሰረት ዶ/ር ቃልኪዳን በአብላጫ ድምፅ ሴክረታሪ ሆነው ተመርጠዋል፡፡


· ለፋይናንስ የታጨ ባለመኖሩ ከኮሚቴው አባላት ውስጥ በአጠቃላይ ድምፅ ተሰጥቷል

o ዶ/ር ቃልኪዳን - 0 ድምፅ

o ዶ/ር ሰናይት - 9 ድምፅ

o ዶ/ር ሊዲያ - 3 ድምፅ

o ዶ/ር ሰላማዊት - 12 ድምፅ

o ዶ/ር ፍረወይኒ - 7 ድምፅ

o ዶ/ር አዜብ - 2 ድምፅ

o ዶ/ር ነቢያት - 1 ድምፅ

o ዶ/ር ኤደን - 2 ድምፅ አግኝተዋል፡፡

በዚህም መሰረት ዶ/ር ሰላማዊት በአብላጫ ድምፅ ፋይናንስ ሆነው ተመርጠዋል፡፡


Ø በንዑስ ኮሚቴ ስር ለመሆን በሚሰራው ቡድን ውስጥ ሁሉም ፈቃደኛ ኢንተርኖች እንዲካተቱ ተወስኗል፡፡


በመቀጠል የመድረክ መሪዋ በመቀጠል የሚቀርበውን ጥናታዊ ፅሁፍ ርእስ “Experience of other medical women’s association” አስተዋውቀው አቅራቢዋን ዶ/ር ፍረወይኒን ወደ መድረክ ጋብዘዋል፡፡


ዶ/ር ፍረወይኒ አለም ላይ ያሉትን ማህበራት እነማን እንደሆኑ በመዘርዘር ለምሳሌነት የሚጠቀሱትን በስፋት አብራርተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል፡-


o Medical Women’s International Association

§ 90 የአለም ሀገራት የሚወክል ማህበር ሲሆን የመጀመሪያ ስብሰባውን በኒውዮርክ በ1919ዓ.ም አካሂዷል፡፡ በወቅቱ ከ16 ሀገር የተውጣጡ ዶ/ሮች ማህበሩን ተቀላቅለዋል፡፡ ዋና መወመጫውም ስዊዘርላንድ ይገኛል፡፡ ማህበሩ 11 የአፍሪካ ሀገራትን ሲያካትት ኢትዮጵያ ግን እካሁን ድረስ አባል አይደለችም፡፡ ነገር ግን አባል ለመሆን የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ ነው፡፡ የማህበሩ ዋና አላማ ዘር ሳይለይ በሙያው ውስጥ ያሉ ሴቶችን ማቀራረብ እና አብረው እንዲሰሩ ማስቻል ነው፡፡ በተያያዘም በአለም ላይ በሚፈጠሩ ፆታዊ፣ ሰብዓዊ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ይሰራል፡፡ ከአለም አቀፉ የጤና ድርጅት ጋር ቀጥተኛ የስራ ግንኙነት ያለው ማህበር ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው የእኛ ማህበር ከአለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር ቢሰራ እንዴት መፍትሄዎችን በቶሎ ማግኘት እንደሚቻል ነው ፡፡ በተጨማሪም ማህበሩ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በመስራት በፅሁፍም የተቀመጡ ብዙ ማስረጃዎች እና ማጣቀሻዎች እንደሚያዘጋጅ አብራርተዋል፡፡


o American Medical Women’s Association

§ የተቋቋመው በ1950 ሲሆን የህክምና ሙያተኞችን እና ተማሪዎችን ያካተተ ማህበር ነው፡፡ በአጠቃላይ ከ3000 በላይ አባላት አሉት፡፡ ማህበሩ የሴቶች ሙያ ብቃት ማሻሻያ እና ጤና ላይ አተኩሮ ይሰራል፡፡ በተጨማሪም የስነ ተዋልዶ ጤና ትምህርት ላይ በጥልቀት ይንቀሳቀሳል፡፡ እንዲሁም የተለያዩ ፅሁፎችን የማሳተም እና ለሙያተኞች እውቅና የመስጠት ፕሮግራም ያካሂዳል፡፡ ይህንን የመሳሰሉ ስራዎች ልምድ መውሰድ አለብን ብለዋል፡፡ አያይዞም የአሜሪካው ማህበር አባላት የሙያ ብቃት ያሳድጋሉ፣ ከአለም አቀፍ ባለሙያዎች ጋር ይገናኛሉ፣ እገዛ እና ድጋፍ ይደረግላቸዋል፣ የነፃ ትምህርት እድልም ይሰጣቸዋል ስልጠናዎችንም ይሳተፋሉ፡፡


o American Women’s Hospital Services

§ እንደ ማህበር ከሀገራቸው አልፈው ሌሎችን እየረዱ ከሚገኙ እና እኛም አላማቸውን መከተል ከሚኖርበብን ማህበር አንዱ ነው፡፡ ማህበሩ አለም ላይ ያሉ በገጠርም ሆነ በከተማ ያሉ ሆስፒታሎችን ድጋፍ የሚሰጥ ሲሆን ኔፐል ውስጥ የራሳቸውን ክሊኒክ ከፍተው ከ50000 በላይ አቅም የሌላቸውን ታማሚዎችን በነፃ ያገለግላል፡፡ በተመሳሳይ ዩጋንዳ ውስጥም ክሊኒክ ከፍተው እያገለገሉ ሲሆን የነፃ ትምህርት እድል ለተተኪው ትውልድ ያመቻቻሉ፡ በአሁኑ ሰኣት በአመት ከ50000 ድረስ ሰዎችን በማከም ይገኛሉ፡፡


o Medical Women’s Federation

§ በ1879 በለንደን የተቋቋመ ሲሆን 9 አባላት ብቻ ነበሩት፡፡ በ1917 እንደገና በድርጅት መልክ ተቋቋሞ 190 አባላትን አካቷል፡፡ በተላላፊ በሽታዎች፣ በወሊድ ዙሪያ፣ በአመጋገብ፣ ጤና፣ ቅድመ ካንሰር፣ በሴቶች ግርዛት እና በስነ ፆታ ትምህርት ላይ በስፋት የሚሰራ ተቋም ነው፡፡


o Medical Women’s Association of Nigeria

§ ሴት ጠቅላላ ሀኪሞችን እና የጥርስ ሀኪሞችን ያካተተ ማህበር ሲሆን በ1977 የተመሰረተ ነው፡፡ መስራቿ Dr. Soludayisi Oduntan የMWIA ስብሰባን ከተካፈሉ በኋላ ሀገራቸው ተመልሰው የመሰረቱት ማህበር ነው፡፡ ከዚህ በጥቂቱ የምንማረው ነገር ማህበራችን በተቻለ መጥ በሁሉም ዘርፍ ያሉ ሴት ሀኪሞችን ማካተት እንዳለበት ነው ፡፡ ናይጄሪያ አለም አቀፉን ማህበር በ1976 ተቀላቅላለች ይህም በአፍሪካ የመጀመሪያው ሀገር ያደርጋታል፡፡ ይህንን ተከትሎ ማህበሩ ከተለያዩ ማህበራት ጋር አብሮ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ አቅማቸውን በማጎልበት 31 ቅርንጫፎችን ለመክፈት በቅተዋል፡፡ ከዚህ ልምድ በመነሳት እኛም በአንድ ቦታ ብቻ ተወስነን ሳንቆም በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ቅርጫፎችን መክፈትና አቅማችንን ማደራጀት ይኖርብናል ብለዋል፡፡ የናይጄሪያው ማህበር በእናቶች እነ በህፃናት ጤና ላይ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ያደርጋል አባላቱም የጤና ፖሊሲ ጥናት ላይ እንዲሳተፉ እድል ያመቻቻል፡፡ እኛም በእቅዳችን ውስጥ ያካተትነው ነገር ስለሆነ ጠንክረን ብንገፋበት ሌሎቹን ነገሮች በስሩ ማሳካት እንችላለን በማለት ፅሁፋቸውን አጠቀናዋል፡፡


በመጨረሻም መድረክ መሪዋ ዶ/ር ፍረወይኒን አመስግነው የጠቀሱትን ሀሳቦች በኢሴሃማ በእቅድ ደረጃ የተቀመጡ ነገሮች መሆናቸውን እና ወደፊት ገፍቶ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በዚህም በቀረበው ጥናት ላይ ኢመዋ ምን አይነት ነገሮችን መስራት እና ማሰብ እነዳለበት አባላት እንዲወያዩ መድረኩን እንዲመሩ ዶ/ር ብዙነሽን ጋብዘዋል፡፡


ዶ/ር ብዙነሽ ለአባላት ምስጋና አቅርበው ዶ/ር ፍረወይኒ በሰጡት ገለፃ ላይ አጠር ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ ሀገራት ማህበራት አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ 100 አመታት ማስቆጠራቸውን አውስተው በእኛ ሀገር ደረጃ ግን ብዙ መሰራት ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ውስጥ ከህክምና ማህበር ውጪ ብዙ ማህበራት መኖራቸውንና ኢመዋ አቅጣጫው በሴቶች ላይ ቢሆን ቅድሚያ ምን ጉዳይ ላይ መስጠት አለብን የሚለውን መወያየት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡ይህንንም መሰረት ባደረገ አባላት ሀሳብ እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡


ውይይት

ዶ/ር ሊዲያ

· ከቀረበው ጥናት ላይ ምን ልንማር እንችለለን፤ በሚቀጥለውስ የትኞቹን ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥተን እንሰራባቸዋለነ የሚለው እንደ ማህበር ለመወያያ መነሻ ቢታሰብ ከዚህ በኋለ እቅዳችን ወዴት እንደሚያመራ ለማወቅ ይጠቅመናል ብለዋል፡፡ በመቀጠልም በአለም ላይ አንዲሁም ከተለያዩ ማህበራት ከትውልድ ትውልድ የሴቶችና የሀኪሞች ላይ የሚነሳው ጉዳይ ተቀራራቢነት እንዳለው ገልፀው፡፡ ሴቶች ራሳቸውን ከአደጋ መጠበቅ/መከላከል በተለይም በጤና ዘርፍ ላይ ያሉ ሴቶች መብት ማስከበር በጣም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ተቀባይ ብቻ ሳይኮን ለሌሎችም ምን ማድረግ እንችላለን የሚለው ጉዳይ በረጅም ጊዜ እቅድ መታሰብ እንዳለበት ሀሳብ ሰተዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የሴቶችን ጤና ለማስፋፋት የተጀመሩ ሙከራዎች እንዳሉ እና በጥልቀት ማስቀጠል እነዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በተያያዘም ከሌሎች በታየው ልምድ መሰረት አባላት እርስ በእርስ መደጋገፍ እንዳለባቸውና አዲስ ተመራቂዎችም ከነባሮች የተሻለ ልምድ በመውሰድ ጥሩ መንገድ እንዲጀምሩ የሚያደርግ አሰራር እንዲሁም ሴት ሀኪሞችን ወደ አመራርነት ማብቃት የሚቻልበት መንገድ ቢመቻች ተገቢ ነው ብለዋል፡፡


ዶ/ር መቅደስ የሚከተሉትን ሀሳቦች አንስተዋል

· ባለፈው አመት ለውይይት የቀረቡት አጀንዳዎች ማንሳትና መወያየት እነደሚያስፈልግ ገልፀው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ምን መስራት እንችላለን የሚለው ማንሳቱ አስፈላጊ ነው ፡፡ በአሀን ሰአት ሀገራችን ላይ መብታችንን የመጠየቅ እድሉ ሰፊ መሆኑን ከቀደመው ስርአት ጋር አነፃፅረው አስረድተዋል፡፡ የሚነሱት ሀሳቦች እና ጥያቄዎች መደጋገም እንዳይመጣ የትኩረት አቅጣጫንን እኛ መስራት የምንችለው ጉዳይ ላይ ብናደር ምክንያቱም አብዛኞቹ እየተነሱ ያሉት ሀሳቦች በሌሎች ድርጅቶች እቅድ ውስጥ ያሉ እና በእነሱ የሚሸፈን ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡ ነገር ግን እንደ ማህበር የሚነሱት እቅዶች ላይ ምን የተለየ ተሳትፎ እናረጋለን የሚለው ተለይቶ ቢቀመጥ የተሻለ ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

· ለአዲስ ተማሪዎች እገዛ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ከሌሎች ሀገራት ልምድ ጋር አወዳድረው አስረድተዋል፡፡ ስለዚህም ማህበሩ የሚቀጥለውን ተረካቢ ለማፍራት አሁን ላይ በተለየ መልኩ እውቀትና ችሎታ እንዲያዳብሩ ብንሰራ ሌሎችን ለመሳብ ያስችለናል ብለዋል፡፡

· የተለያዩ ቅስቀሳ ማካሄድ፣ ስልጠና ማድረግ፣ የማሳወቅ እና የማበልፀግ ስራዎች በስፋት መሰራት አለባቸው የሚል ሀሳብ ሰተዋል፡፡


ዶ/ር አዜብ በበኩላቸው እነዚህን ሀሳቦች ሰንዝረዋል፡፡

· የአባላት መብትና ግዴታ ምን እንደሆነ መለየት ያስፈልጋል፡፡ አባላትን በክፍያ ማካተታችን እንዳለ ሆኖ አሁንላይ 50 ብቻ ነን፡፡ ነገር ግን በሀገራችን ምን ያህል ባለሙያ እንዳለ ታሳቢ ተደርጎ እነሱንም ተደራሽ ማድረግ አለብን፡፡

· ብዙ ማህበራት በጎ ጎናቸው የባለሙያዎች መዝገብ ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ የትኛው ባለሙያ ምን እንደሚሰራ እና የት እንደሚገኝ ለማህበረሰቡ በሚዳረስ መልኩ ማደራጀት ይኖርብናል ይህንንም ስናደርግ አጋር ድርጅቶች ለማግኘት ጥሩ እድል ይፈጥርልናል፡፡

· አለም አቀፍ ማህበራትን ለመቀላቀል ከእኛ የሚጠበቀው ምንደነው የሚለውን ማጥናትና ማወቅ አለብን፡፡ ከቅርብ ካሉት የህክምና ተማሪዎች ማህበር እንደ ምሳሌ ወስደን ማየት እንችላለን፡፡

· ስለ ፆታዊ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን በሙያችን ዙሪያ እርስ በእርስ የምንደጋገፍበት እና የምንወያይበት መድረክ ቢኖር በስራ ላይ የሚያጋጥሙንን እክሎች እንድንቀርፍ ያስችለናል፡፡

· ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሁለት ነገሮችን መርጠን በስፋት ብንሰራ ውጤታማ ያደርገናል፡

· በቀላሉ የምትዘጋጅ መፅሄት ብንጀምርና የተለያዩ ፅሁፎችን እየሰበሰብን ብናዘጋጅ ከማህበረሰቡ ጋር እንዲሁም እርስ በእርስ ያቀራርበናል፡፡

· የፋይናንስ አቅማችንን ለማሳደግ አጋር ድርጅቶችን የምናመጣበት የተለየ እቅድ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ አያይዞም የረጅም እና አጭር ጊዜ እቅድ መታሰብ ይኖርበታል ብለዋል፡፡


ዶ/ር ሰላማዊት

· ፆታ ተኮር የሆነ ሴቶችን ማዕከል ያደረገ የጤና ፖሊሲ ያስፈልገናል፡፡ ሀገራችን አሁን ቅድመ መከላከልን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ ነው የምትከተለው ነገር ግን የሴቶች የእድሜ ጣራ ከወንዶች የበለጠ ቢሆን ለበሽታ የመጋለጥ እድላቸው ግን የሰፋ ነው፡፡ ይህን ታሳቢ ያደረገ ፖሊሲ ያስፈልገናል፡፡ በዚህ ዙሪያ የሚሰሩ ባለሙያዎች ጫና እንዲያደርጉ ማህበሩ ሰፊ ስራ መስራት አለበት፡፡ በተጨማሪም እያንዳንዱ ሴት ለራሷ መብት ጠበቃ መሆን አለባት ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል ህክምና ላይ የሚደረጉ ማንኛውም እንቅስቃሴዎች ከየትኛውም ጫና የፀዱ መሆን አለባቸው በማለት በአማራ ክልል የተከሰተውን እንደምሳሌ በማንሳት ማህበሩ ጠንከር ያለ ሀላፊነት ወስዶ ያለውን ጫና የመቀነስ ስራ መስራት አለበት ብለዋል፡፡ ማንኛውም እንቅስቃሴ የሴቶችን መብት ሳይጋፋ ግን ሙያዊ ድጋፍ በታከለበት ትምህርት እየተሰጠ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ተሳታፊ እና የአይደር ሜዲካል ማህበር አባል (ከመቀሌ)

· የጤና ባለሙያዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገር አቀፍ ደረጃ ብዙ ጥያቄዎችን አንስተው ሲጠይቁ እና መንግስትም በምላሹ ለማወያየት በሞከረበት ወቅት እንኳን ለኢመዋ አባላት ወይም እንደ ማህበር ጥሪ አልቀረበለትም/ አልተጋበዘም ነበር፡፡ ማህበሩ እንዳለ ካለማወቅ ነው ወይስ ምክንያቱ አልታወቀም፡፡ ንቁ እንቅስቃሴ ብናደርግ ትኩረት ይሰጠን ነበር፡፡ በመንግስት ፖሊሲ ላይ ለመሳተፍ ከፈለግን እየተንቀሳቀስን በክልልም ቅርንጫፎችንም እያበዛን እንደሆነ መንግስት ማወቅ አለበት የሚል አስተያየት ሰተዋል፡፡

ዶ/ር  ሁስኒያ

· መብታችንን ከመጠየቃችን በፊት ምን ያህል ጠንካራ እንደሆንን ማሳየት አለብን ፡፡ እቅዶችንም መሬት ለማውረድ እውቅናችንን ከፍ ማድረግ ይኖርበናል ብለዋል፡፡


ዶ/ር መቅደስ በድጋሚ የሚከተለውን ሃሳብ አክለዋል

· ፖሊሲውን በተመለከተ እንደ ማህበር ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑን አስረድተው የፆታ ጉዳይ እንዲካተት ተፅዕኖ በመፍጠር እየተሞከረ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በአስተዳደራዊ ጉዳይ ምክንያት በድጋሚ ከፖሊሲው እንደተቀነሰ እና መብታችንን ለማስከበር በጋራ መንቀሳቀስ አለብን በማለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

· ሚዲያ ላይ በስፋት መሰራት እንዳለበት ጠቁመው በጊዜ ጥበት እና በሀላፊነት መደራረብ ምክንያት ትኩረት እንዳልተሰጠው በመግለፅ ማህበራዊ ሚዲያን እንደ አማራጭ መጠቀም ለመረጃ ፍሰትም ለአጠቃቀምም የተሻለ መንገድ ይፈጥርልናል ብለዋል፡፡ መረጃዎችንም አባላት በእኩል ሼር ማደረግ እንዳለባቸው ጠቅሰዋል፡፡


ዶ/ር ብዙነሽ የተሰጡትን አስተያየት መነሻ በማድረግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ብዙ ስራ መስራት አለበት እንዲሁም የማህበሩን እውቅና ለማሳደግም እየተንቀሳቀስን እንደሆነ በማስተዋወቅ መሰራት አለበት ብለዋል፡፡ማህበሩ ለአባላት ምን ማድረግ ይችላል ተብሎ ለተነሳው ሀሳብም የሚከተሉትን ነጥቦች ዘርዝረዋል፡፡

o የአባላት ምዝገባ ማካሄድ

o የባለሙያዎች መዝገብ ማዘጋጀት እና የሚደጋገፉበትን መድረክ ማመቻቸት

o አባላትን ወደ አመራርነት ማብቃትና የተለያዩ የክህሎት እና ብቃት ማሻሻያ ስልጠና መስጠት

o አባለት ችግር በሚያጋጥማቸው ጊዜ የሚረዳቸው እና የሚያግዛቸው ራሱን የቻለ ኮሚቴ መፍጠር እንዲሁም ሀገሪቷ ላይ የወጡትን ህጎች የሚያስከብር ስርዓት መዘርጋት

o ለአባለት ያልተቋረጠ ብቃት ማሻሻያ ስልጠና ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር መስጠት

o የህግ ከለላ መስጠት ባይቻልም ከህግ ጠበቆች ጋር በመነጋገር በስነ ተዋልዶ መብቶች ላይ ማን ሀላፊነት ወስዶ እንደሚሰራ አጥንቶ መንገድ ማበጀት፡፡ በሀኪም ቤት ደረጃ የሚሰጠውን አገልግሎት እንዲስፋፋ በማድረግ ማህበረሰቡም አገልግሎቱን የት እንደሚያገኝ በማስተማር እንዲሁም የአገልግሎት ጥራቱን በመቆጣጠር ተጠያቂነት ያለው አሰራር መፍጠር አና በህክምናው ዘርፍ ለው ችግር ለይቶ በማውጣት መንቀሳቀስ አለበት፡፡

o ፖሊሲን በተመለከተ የተሻሻለው ፖሊሲ ሀሳብ እንድንሰጥበት መላኩን ገልፀው አባለት ተመልክተውት የሚሰጠውን አስተያየት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ለጤና ጥበቃ በማስተላለፍ ድምፃችንን ያሰማል በተጨማሪም ፖሊሲው ላይ የሚካተቱት ነገሮች እንዴት ወደ ስራ እንደሚተገበሩ መታሰብ ይኖርበታል ብለዋል፡፤


በአጠቃላይ የተሰኑትን ሀሳቦች ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ እንደሚመሩት ገልፀው አዲሱ ኮሚቴ በአመት ውስጥ በስሩ የተለያዩ ንኡስ ኮሚቴ ስለሚያዋቅር አባላት ንቁ ተሳትፎ እንዲያረጉ ጥሪ በማቅረብ ውይይቱን ዘግተዋል፡፡


በመቀጠልም መድረክ መሪዋ የመጨረሻ ይልተነሳ ሀሳብ አለን ለሚሉ አባላት እድል ሰጥተዋል፡፡

ዶ/ር  ሙና 

· ከዚህ ቀደም በማህበሩ ስም ሲደረግ የነበረው የደም ልገሳ ፕሮግራም በየ 3 ውሩ ሳይቋረጥ የሚካሄደበት ሁኔታ ቢመቻች ለሌሎችም አርአያ እንሆናለን ብለዋል፡፡ ከህክምናውም ባሻገር ለሀገራችን ሰላም ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የሚል መልእክት አስተላልፈዋል፡፡


ዶ/ር ቤዛዊት

· ከዚህ በይበልጥ እና በስፋት የህክምና እርከን ላይ ያሉትን በማሰባሰብ ሰፋ ያሉትን በማሰባሰብ ሰፋ ያለ ጉባኤ ቢዘጋጅ እና ተሳታፊዎች አስበውበት እና ተዘጋጅተው መወያየት ቢቻል። እንዲሁም የአገሪትዋን ሰላም ለማስጠበቅ የበኩላችንን አስተዋፆ ማድረግ ይገባናል ብለዋል።


የመድረክ አስተዋዋቂ ዶ/ር ነቢያትም በማጠቃለያነት በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ስብሰባውን አስመልክቶ ጥሪ ያስተላለፈ ቢሆንም የተገኘው አባል ግን በጣም ትንሽ ነው፡፡ ከ230 ባላይ እንመጣለን ብለው ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም ጠዋት የመጣው ሰው በማየት ስብሰባውን ለሌላ ቀን ለማስተላለፍ ታስቦ እንደነበር እና በብዙ ግፊት መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡ ስብሰባው የግድ ያስፈለገበት ምክንያት ማህበሩ እስከ አሁን ለ2 አመት ቋሚ ባልሆነ ስራ አስፈፃሚ ሲንቀሳቀስ ሰለነበር እንደማህበር በየአመቱ መደረግ የነበረበት ጠቅላላ ጉባኤ ሳይካሄድ በመቆየቱ ስብሰባው በመጣው ሰው ሊቀጥል ችሏል ብለዋል፡፡ ማህበሩም አባላት በፈቃዳቸው የመረጧቸው ሰዎችም እንዲመራ ሆኗል፡፡ ለመጪው ጊዜ በየወቅቱ አነስተኛ ስብሰባ በማድረግ መረጃዎች የሚተላለፉበት መንገድ ይዘጋጃል የሚል ማረጋገጫ ሰተዋል፡፡ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ሀላፊነት ወስዶ እንደሚሰራ አፅእኖት ሰተው፡፡ አባላትም ልዩ ድጋፍና ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡ የአባልነት ክፍያም በማህበሩ ጽ/ቤት በመሄድ እንዲከፍሉና መታወቂያ እንዲወስዱ አሳስበዋል፡፡


ዶ/ር ብዙነሽ በማጠቃለያነት የተነኡትን ሃሳቦች ለስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው እምደሚመሩት ገልፀው አዲሱን ኮሚቴ በአመት ውስጥ በስሩ የተለያዩ ንኡስ ኮሚቴ ስለሚያዋቅር አባላቱ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርርጉ ጥሪ በማቅረብ ውይይቱን ዘግተዋል።


በመጨረሻም የማህበሩን ፕረዝዳንት ዶ/ር ሀይማኖት የመጨረሻ ንግግር እንዲያደርጉ ጋብዘዋል፡፡


ዶ/ር ሀይማኖት በስብሰባው ላይ የተገኙት አባላት አመስግነው የተነሱት ሀሳቦች ጥሩ መሆናቸውን ማህበሩ ብዙ ሰርቶ ሳይሆን በትንሹ የመጀመሪያውን መስመር እንደሄደ እና ከዚህ በጓላ ብዙ ለመስራት ከጉባኤው የሚገኘውን ሀሳብ ግብአት በማድረግ ወደላቀ ደረጃ ለመድረስ ነው፡፡ ከአዲሱ ስራ አስፈፃሚ ብቻውን ሳይሆን እያንዳንዱ አባል አስተዋፅኦ ወሳኝ እነደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም እንደ ሀሳብ ኮሚቴው በየ3 ወሩ የተሰሩትን ስራዎች ሪፖርት ቢያደርጉ አባላትም ክትትል በማድረግ እንዲሁም ጥያቄ ቢጠይቁ ተጣያቂነት ይኖራል ብለዋል፡፡ ምን እንደተሰተራ እና ምን እንደቀረ ለመከታተል ያመቻል በማለት ሁሉንም ተሳታፊ አመስግነዋል፡፡ ዶ/ር ብዙነሽን ለሚያደረጉት እገዛ ምስጋና አቅርበውላቸዋል፡፡

ስብሰባውም ከቀኑ 10፤00 ሰአት አብቅቷል


 
 
 

Comments


bottom of page